የአማራ ክልል ምክር ቤት ሴቶች ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተሏቸውን የትምህርት ቢሮ፣ የጤና ቢሮ፣ የሴቶች ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና የሲቪልና ቤተሰብ አገልግሎት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።
የተቋማቱ የሥራ ኀላፊዎች የተቋማቸውን አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል። ቋሚ ኮሚቴውም የቀረበውን ሪፖርት በመከታተል አስተያየት እና ጥያቄዎችን ያነሳ ሲኾን ሪፖርቱን ያቀረቡ የተቋማቱ የሥራ ኀላፊዎች ምላሽ ሰጥተውባቸዋል።
በክልሉ ምክር ቤት የሴቶች ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ አበራሽ ታደሰ በጀት ዓመቱ ኹሉም ተቋማት ያቀዷቸውን ተግባራት ከመፈጸም፤ ከበጀት አጠቃቀም፤ ከኦዲት ግኝት ፤ ከተሻጋሪ ሥራዎች እና ከሌሎች ተግባራት አኳያ ውጤታማ ሥራ ያከናወኑበት ዓመት መኾኑን ተናግረዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በተቋማቱ አፈጻጸም በጥንካሬ የተከናወኑ እና ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸውን እንዲኹም በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን አንስቷል።
🔥 ቋሚ ኮሚቴው ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ካላቸው የተቋማቱ ውጤታማ አፈጻጸሞች መካከል፦
👍 የክልሉ ትምህርት ቢሮ ዲጅታላይዜሽን እና መሰል የለውጥ ሥራዎችን ከመተግበር አኳያ ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል ብሏል። የትምህርት ሥራውን እስከታች ወርዶ ከመደገፍ አኳያም ውጤት የተገኘበት ሥራ መሠራቱም ተነስቷል።
የተማሪዎች ምዝገባ ላይ ከዕቅድ አኳያ ብዙ የሚቀር ቢኾንም ከባለፈው ዓመት አኳያ የተሻለ የተማሪዎች ምዝገባ መከናወኑ፤ አዳሪ፣ ሞዴል እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ ለማስጨረስ እንዲኹም ለፈጠራ እና ለምርምር የተሰጠው ትኩረት የሚበረታታ መኾኑም ተነስቷል።
የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለኾኑ ተማሪዎች የተከናወነው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፤ የምገባ አገልግሎት እና መሰል በጎ ተግባራት ውጤታማ ቢኾኑም በዕቅዱ ልክ ለመፈጸም ጥረት መደረግ እንዳለበትም ተመላክቷል። የቁሳቁስ ድጋፍ ፍትሐዊነት እና የምገባ ዕቅድን ከመፈጸም አኳያ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ተብሏል።
✨ የክልሉ ጤና ቢሮ በርካታ ሥራዎች ያከናወነበት እና የተዋረድ ተቋማት ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ ጥሩ መነሳሳት የተፈጠረበት ዓመት ማሳለፉ ተነስቷል።
ጤና ቢሮው የኢኒሸቲቭ ተግባራትን በመፈጸም፤ ባለሙያን በማብቃት፤ ይነሱ የነበሩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመፍታት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው ተብሏል። ጤና ቢሮን መልሶ በመገንባት ምቹ የሥራ ከባቢን ከመፍጠር እና የጤና ተቋማትን ከመገንባት አኳያም አመርቂ ሥራ መከናወኑ ተገልጿል።
የሕክምና መሣሪያዎችን የማሟላት፤ የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቶች በመገንባት ማኅበረሰቡ በቅርበት የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የተከናወነው ሥራም የሚበረታታ መኾኑ ተነስቷል።
✨ የሴቶች ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ፈጻሚ ተቋም ባይኾንም ብዙዎቹ ተግባራቱ ውጤታማ እንደኾነ ተገልጿል። ዓለም አቀፋዊ በዓላትን በማክበር ግንዛቤ የመፍጠር፤ ድጋፍ የሚፈልጉ ሴቶችን እና ሕጻናትን ከመደገፍ፤ የሴቶች ኅብረትን ከማጠናከር እና ብድር ከማቅረብ አኳያ ጥሩ መሠራቱ ነው የተገለጸው።
✨ ሲቪልና ማኅበረሰብ አገልግሎት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ፤ ከተቋማት ጋር የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማስፋት፤ የበይነ መረብ ምዝገባን ከመዘርጋት እና መሰል የተከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ መኾናቸው ተነስቷል።
ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ በተቋማቱ ትኩረት እንዲሰጣቸው ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከልም፦
✨ ትምህርት ቢሮ አሁንም ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ በርካታ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ርብርብ ማድረግ ይገባዋል ተብሏል።
ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ተሳትፎ፤ ለአካል ጉዳተኞች ክፍያ እና ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤ ለጎልማሶች ተግባር ተኮር ትምህርት፤ ከደረጃ በታች የኾኑ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ተብሏል።
የሕጻናት እና አካል ጉዳተኞች የአዕምሮ ዕድገት እና የግብረ ገብ ትምህርት ላይ በቂ ሥራ ስላልተሠራ ቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመላክቷል።
✨ ጤና ቢሮ የኅብረተሰብ ተሳትፎን ማጠናከር ፤ የሆስፒታል ሽፋንን ማሳደግ፤ በቂ መድኃኒት ማቅረብ፤ የሆስፒታሎችን ደረጃ ማሻሻል ላይ ቀጣይ ትኩረት ያስፈልጋል ተብሏል። የሕክምና መሣሪያዎችን ከብልሽት የመከላከል እና አፋጣኝ ጥገና በማድረግ ተገቢ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም የቤት ሥራ ተሰጥቷል።
✨ የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊትን ከመከላከል፤ የሕጻናት የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ የመፍጠር እና የሴቶችና ሕጻናትን ጥቃት መከላከል ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስተያየት ተሰጥቷል።
✨ የሲቪል እና ቤተሰብ አገልግሎት አሠራሮችን ከሙስና እና ብልሹ አሠራር የማስወጣት ሥራ በቀጣይ ትኩረት ያስፈልገዋል ተብሏል።
በጥቅሉ በ2018 ዓ.ም ተቋማት በዕቅዳቸው ልክ ለመፈጸም ያደረጉት ርብርብ እና የተገኘው ውጤት ካለፉት ዓመታት አኳያ የተሻሉ ውጤቶች የተመዘገቡበት መኾኑ ተነስቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *