ሐምሌ 21/2018ዓ.ም(ትምህርት ቢሮ)የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የድጋፍና ክትትል ቡድን በደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ያደረገውን የድጋፍና ክትትል ግብረ መልስ የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት የተደራጀ ግብረ መልስ ሰጥቷል፡፡
የድጋፍና ክትትል ግብረ መልሱን ያቀረቡት አቶ ምስጋነው ብርሐኑ እንደገለጹት በከተማ አስተዳደሩ ያሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ቤት መሻሻል እቅድ፣ የክረምት ስራዎች እቅድ በማቀድ፣ በክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ ግብዓት ለማሟላት፣ አረንጓዴ አሻራ ስራዎች፣የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል እያደረጉት ያሉት እንቅስቃሴዎች አበረታች በሆናቸውን አንስተዋል፡፡ በቀጣይ መስተካከል አለባቸው ያሏቸውን ነጥቦች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሐን አንተነህ እንደተናገሩት የክልሉ ትምህርት ቢሮ የድጋፍና ክትትል ቡድን ያደረገውን ድጋፍ ለቀጣይ ስራቸው እንደ አቅም ወስደው በተሟላ ሁኔታ ወደ ተግባር እንደሚቀይሩት አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያና የቀጣይ ትኩረት ነጥቦችን ያስቀመጡት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን እንደገለጹት በታዩ ትምህርት ቤቶች የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ማስፋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤቶች ወመህ ተጨማሪ ክፍሎችን ለማስገንባት በድጋፉ ወቅት ሲሰሩ ማግኘታችን ማህበረሰቡ ትምህርት ቤቶችን በባለቤትነት እየደገፈ መሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም በትምህርት ቤቶች የተጀመረውን የማጠናከሪያ ትምህርት፣ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማሰባሰብ ስራ፣ የመማሪያና ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች እድሳትና ጥገና፣ የትምህርት ቤት ምገባ ስራ ግንዛቤ ፈጠራና ሀብት ማሰባሰብ ስራ፣ በትምህርት ቤቶች አረንጓዴ አሻራ ስራዎችን፣ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ራስ ማስቻልና በአዲስ መገንባት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አቶ ጌታቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡



