አሸባሪው የህውሐት ቡድን በወረራ ይዞ በቆየባቸው አካባቢዎች ላይ ትምህርት ቤቶችን በማውደምና በመዝረፍ የጭካኝነትና የክፋተኝነት ጥግ ማሳየቱን ትምህርት ሚኒስትሩ ኘሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ፡፡
የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴርና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አመራሮች በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ በአሸባሪው የህወሐት ቡድን የወደሙና ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ጎብኝተዋል፡፡
አሸባሪው የህወሐት ቡድን የትምህርት ተቋማትን ኮምፒውተሮች: ፕላዝማ ቴሌቬዥኖች፡ የቤተሙከራ ኬሚካሎችና ቁሳቁሶች፡ ወንበሮችና መጽሐፍትን ዝርፏል ቀሪውን አውድሟል፡፡ ትምህርት ቤቶችን በከባድ መሳሪያ ደብድቧል፡፡ የጅምላ ቀብር አድርጓቸዋል፡፡


ትምህርት ሚኒስትሩ ኘሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማትን ከጎበኙ በኋላ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ትምህርት ቤቶችን ከመዝረፉ ባለፈ ድጋሚ አገልግሎት እንዳይሰጡ በማሰብ ማውደሙ የጨካኝነትና የክፋተኝነት ጥግ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡


በሽብር ቡድኑ ከፍተኛ የንብረት ዘረፋና ውድመት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት ደረጃቸውን ባሟላ መልኩ እንደገና መልሶ ለማቋቋም የፌዴራልና የክልል መንግስት ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር ተባብረውና ተጋግዘው ትምህርት ቤቶችን ከነበሩበት በተሻለ መልኩ እንደሚገነቡ እምነታቸው መሆኑንና የትምህርት ሚኒስትሩም ለዚህ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ወራሪውና አሸባሪው የትግራይ ሃይል በትምህርት ቤቶች ላይ አስከፊ ውድመት በመፈጸም በትክክል ከወራሪ የሚጠበቅ ተግባሩን አስመስክሯል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ማተብ ታፈረ ናቸው፡፡ አሸባሪና ወራሪው ሃይል በትምህርት ቤቶች ላይ በመማሪያ ክፍል ሳይቀር የጅምላ መቃብር በመፈጸም በትውልዱ ውስጥ መጥፎ ታሪክ ጥሎ እንደሄደም ገልጸዋል።
ዶክተር ማተብ ታፈረ በአማራ ክልል ከአራት ሽህ በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ ሙሉ በሙሉና በከፊል ውድመት ማድረሱን ገልጸው የቡድኑ አላማ የሚሳካው ትምህርት ቤቶችን በፍጥነት መልሶ ገንብቶ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ ካልተቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከትምህርት ሚንስቴር ጋር በመተባበር መልሶ ግንባታዎች በአጭር ጊዜ እንደሚሰራም ቢሮ ሃላፊው ገልጸዋል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ 912 የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ዝርፊያና ውድመት መድረሱን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጋሻው አስማሜ ተናግረዋል።
አሸባሪና ወራሪው ሀይል በኢትዮጵያ ቀርቶ በአለም ላይ ተደርጎ የማይታወቅ ዘግናኝ ግፍ መፈጸሙን የገለጹት አቶ ጋሻው የወራሪና አሸባሪ ቡድኑ ዋና አላማ በትውልድ ላይ ዘላቂ ጥቃት ማድረስና ማሸማቀቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የወደሙና የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ከ11 ቢሊዬን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና ዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::
በቴሌግራም https://t.me/anrse



