በርካታ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ያሳለፈው የ12ኛክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ይሰጣል፡፡የኮሮና ቫይረስ መስፋፋትና ሌሎች ሰውሰራሽ ምክንያቶች በሀገሪቱ መደጋገማቸውን ተከትሎ ፈተናውን በሚፈተኑ ተማሪዎች ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡
በባህርዳር ከተማ አስተዳደር የጣናሀይቅ አጠቃላይ 2ኛ ደረኛ ት/ቤት ተማሪው ቅዱስ ዋሴ እና በፋሲሎ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዋ ሀና ሰለሞን የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ከፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈተኞች ናቸው፡፡ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአለም አቀፍ ደረጃ መስፋፋቱን ተከትሎ መንግስት ፈተናው የሚሰጥበትን ቀን እና ፈተናው የሚሰጥበት መንገድን መቀያየሩን አስረድተዋል፡፡ ፈተናውን በወቅቱ አለመውሰዳቸው የስነልቦና ጫና ቢያሳድርባቸውም ራሳቸውን ለፈተና እያዘጋጁ መሆናቸውን ነው የነገሩን፡፡
የጣና ሀይቅ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ምክትል ርዕሰ መምህሩ አቶ ፀጋየ ተፈራ በበኩላቸው በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከሰባት መቶ በላይ ተፈታኝ ተማሪዎች በት/ቤቱ እንደነበሩ ገልፀው በ2013 ዓ.ም የመጀመራዎቹ ወራት ተማሪዎችን ለፈተና ለማዘጋጀት የተለያዩ እገዛዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ የማካካሻ ትምህርት በመስጠት፣ አጫጭር ኮርሶችን ፣ጥያቄዎችንና ፁፎችን በማዘጋጀት በበየነ-መረብ አማካኝነት ለተማሪዎቹ ሲሰጡ መቆየታቸውንም አስረድተዋል፡፡
በፋሲሎ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የስነ-ልቦና እና የማማከር አገልግሎት ባለሙያው አቶ የሸአምባው ወርቄም ሀገር አቀፍ ፈተና በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን ተከትሎ ተፈታኝ ተማሪዎቹ ከትምህርት ሂደቱ ለረጅም ጊዜ ርቀው መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጅ ፋሲሎ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርትቤትም ተማሪዎችን ለፈተና ለማዘጋጀት የተለያዩ እገዛዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ነው ያስታወሱት፡፡ በ2013 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢም የስነ-ልቦና ምክርን ጨምሮ የተለያዩ እገዛዎችን ለተማሪዎቹ መስጠታቸውን ተናገረዋል፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የስነ-ልቦና ትምህርት ክፍል መምህሩ ዶክተር አስናቀው ታገለ በበኩላቸው “መጥፎ የሚባሉ አጋጣሚዎችን በማለፍ ለጥሩ ነገር መጠቀም ውጤታማ ያደርጋል ሲሉ ይመክራሉ፡፡ ”ለ12 ዓመታት የተለያዩ ውጣ ውረዶችን በማለፍ የመጡበት የትምህርት ሂደት በፈተና ወቅትም ይዞት የሚመጣ መጥፎ አጋጣሚ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ዩንቨርስቲዎችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርትቤቶች ሲዘጉ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ለመምጣት እና በቂ ቅድመ- ዝግጅት ለማድረግ ምቹ አጋጣሚን ይፈጥራል ሲሉም ዶክተር አስናቀው ምክራቸውን የለገሱት፡፡ ፈተና ይዞት የሚመጣው አዲስ ነገር የለም ያሉት ዶክተሩ የ2012 ዓ. ም ሀገር አቀፍ ፈተና በተለያየ ጊዜ ለመስጠት ቀጠሮ ተይዞለት በተያዘለት ጊዜ ተግባራዊ አለመሆኑ የወደፊት ዘመን ውጤታማነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አለመኖሩን ይገልፃሉ፡፡ ለበቂ ቅድመ ዝግጅት በቂ ጊዜ ከመስጠት ያለፈ ጉዳት እንደሌለውም ምክንያታቸውን ያቀርባሉ፡፡
መንግስት ለመጨረሻ ጊዜ የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ፈተናውን እንደሚሰጥ የገለፀ በመሆኑ ተማሪዎቹ ጊዜአቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙም መክረዋል፡፡ በአሸናፊነት ሰነ-ልቦና ላይ መቆምም ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገርአቀፍ ፈተና 82 ሽ 341 ተማሪዎች ለፈተና እንሚቀርቡ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ሲያስረዳ ከተፈታኞች መካከልም 38 ሽ 845 ተማሪዎች ሴቶች ናቸው ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡-ብናየው ይርሳው (በባህርዳር ዩንቨርስቲ የ2ኛ ዲግሪ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተማሪ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *