በዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል ፈተና የሚወስዱ ሁሉም ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገለጸ።
በጎንደር ከተማ የሚገኘው ፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ለማሳለፍ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ እንዳለው ታደሰ ተፈታኝ ተማሪዎች በቡድን እንዲያጠኑ የማጥኛ ቦታ በማዘጋጀት፣ ያልተሸፈኑ ይዘቶችን በመሸፈን በተመረጡ መምህራን ክለሳ እንዲሰጣቸው በማድረግ፣ አጋዥ መጽሐፍትን በማሟላት፣ በዩኒቨርሲቲ ምሁራን አማካኝነት የስነ ልቦና ስልጠና እንዲወስዱ እና ከዚህ በፊት የተሰጡ ጥያቄዎችን እንዲሰሩ በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ከእያንዳንዱ የተማሪ ወላጆች እና መምህራን ጋር ተማሪዎች ውጤት ለማስመዝገብ በጣሉት ግብ ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ ተማሪዎችን የመደገፍ ስራ እየተሳተራ መሆኑን ርዕሰ መምህሩ ገልጸዋል።
ርዕሰ መምህሩ በዚህ ዓመት የ12ኛ ክፈል ፈተና የሚወስዱ 630 ተማሪዎች ሁሉም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሰራ ነው ብለዋል። ቢያንስ 20 ተማሪዎች 500 እና በላይ ውጤት ለማስመዝገብ ግብ መጣላቸውን ተናግረዋል። ይህን ለማሳካት በውጭ ሀገር የሚኖሩ የቀድሞ ተማሪዎች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አመላክተዋል።
ተማሪ ሱመያ ኢሳ የፋሲለደስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት። በቀጣይ የምትወስደው ሀገር አቀፍ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና 550 እና በላይ ውጤት ለማስመዝገብ አቅዳ እየሰራች መሆኑን ነግራናለች።
ከጓደኞቿ ጋር በጥናት ቡድን በመሳተፍ፣ ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀም፣ የመምህራ እገዛ በትኩረት በመከታተል ላይ መሆኗን ገልጻለች።
ሌላኛው ከጓደኞቹ ጋር በጥናት ቡድን ሲሳተፍ ያገኘነው ተማሪ ናታኔም መለሰ ከ550 በላይ ውጤት ለማስመዝገብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጾ የመምህራን ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀም ከዚህ በፊት በተሰጡ የፈተና ጥያቄዎች በመለማመድ እቅዱን ለማሳካት እየሰራን መሆኑን ነግሮናል። እቅድን ለማሳካት እምነት፣ ቁርጠኝነት እና ተከታታይይ ስራ እንደሚያስፈልግ ተማሪው ገልጿል።
በ1934 ዓ.ም የተመሰረተው የፋሲለደስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለፉት 84 ዓመታት ከ2መቶ 85ሽህ በላይ ተማሪዎችን ማስተማሩን ከትምህርት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን



