የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀሙን በጎንደር ከተማ እየገመገመ ነው።
**********
 የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018ዓ.ም ስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀሙን በጎንደር ከተማ እየገመገመ ነው።
በመድረኩ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ ም/ከንቲባ ወ/ሮ ደብሬ የኋላ እንደተናገሩት ትምህርት የእድገትና ብልፅግና መሠረት መሆኑን ገልፀው በዓለም ላይ ያለው የቴክኖሎጅ ውድድር መሠረቱ ትምህርት መሆኑን ተናግረዋል። ትምህርት የችግር መፍቻ ቁልፉ መሳሪያ ነው ያሉት ኃላፊዋ በክልሉ ትምህርት ላይ ገጥሞን የነበረውን የተሳትፎ፣ ፍትሐዊነት ችግሮች ለመፍታት ሁሉም አካላት ርብርብ ማድረግ አለባቸው ብለዋል። የትምህርት ጉዳይ የማይመለከተው አካል የለም ያሉት ወ/ሮ ደብሬ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ መላ ማህበረሰቡ ትምህርትን ቀይ መስመራችን ነው ብሎ ለጥራቱም፣ ተሳትፎውም፣ ፍትሐዊነቱም መሳካት ርብርብ ማድረግ አለብን ሲሉ አብራርተዋል።
በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ በትምህርት ዘመኑ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ የትምህርት የ25ዓመት አሻጋሪና ዘላቂ የልማት እቅድ፣ የ5 ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ እንዲሁም የ2018 በጀት አመት እቅድ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን፣ እቅዱንንም እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ትውውቅ መደረጉን፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ መድረኮች መካሄዳቸውን፣ ባለፉት ሁለት አመታት ተሳትፎ ላይ የገጠመውን ችግር ለማለፍ የተማሪ ምዝገባ በንቅናቄ ለማስኬድ የተደረጉ ጥረቶችን አንስተዋል። በዚህም የእቅዱን 60% ተማሪዎች መመዝገባቸውን አቶ መኳንንት አደመ ገልፀዋል። በስድስት ወሩ በርካታ የትምህርት ግንባታዎች መሠራታቸውን፣ የትምህርት ቁሳቁሶች መሰብሰባቸውን አንስተዋል። ተማሪዎችን ለማብቃት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አበረታች መሆኑን አቶ መኳንንት አደመ ገልፀዋል። በ2017 ክረምት የአንደኛና መካከለኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንን አቅም ለማጎልበት ስልጠና መሰጠቱን አውስተዋል። በዚህም ውጤት መታየቱን አክለው ገልፀዋል።
በቀጣይ በትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ 153 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ ያሉት አቶ መኳንንት በወረዳዎች በጀት በመያዝ ደግሞ 153 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ አንስተዋል። ይህም የዘርፉን ተሳትፎናፍትሐዊነት እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት አመት የሚጠናቀቁ በክልሉ በጀት ድጋፍ 3 ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን ተጠቅሷል።
የትምህርት ቤት ተማሪዎች ምገባ ኢንሸቲቭ በከተሞችና በብዙ ዞኖች መጀመሩን ጠቅሰው የድጋፍና ክትትል ስራዎቻችን ተስፍ ሰጭ ውጤቶችን እያመጡ መሆኑን ም/ቢሮ ኃላፊው አብራርተዋል።
በግምገማ መድረኩ የማዕከላዊ ጎንደር፣ ጎንደር ከተማ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር እና ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ የዞንና ወረዳ ትምህርት አመራሮች፣ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን
5. በቲክቶክ ገፃችን @amharaeducation bureau

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *