የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት በትጋት እየሰራ መሆኑን የጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ አስታወቀ
የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች በህግ ከተሰጣቸው ኃላፊነቶች መካከል መማር ማስተማር በብቃት በማከናወን ብቁ መምህራንን ማፍራት፣ በጥናት እና ምርምር በመታገዝ መፍትሄ ለሚሹ ጒዳዮች መፍትሄ ማፈላለግ እና የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ዋና ዋናወቹ ናቸው፡፡
አንጋፋው የጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ከተመሰረተበት 1974 ዓ.ም ጀምሮ ከ64 ሽህ በላይ መምህራንን አፍርቷል፡፡የኮሌጁ ዲን አቶ የሺአምበል ፀሐይ ኮሌጁ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኮሌጁ የቅድመ አንደኛ፣ የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ መምህራንን በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡ ኮሌጁ በጎንደር እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለሚገኙ የተመረጡ ትምህርት ቤቶች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ዲኑ አመላክተዋል፡፡ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ ከ1ሽህ 4 መቶ በላይ መምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮች ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ ሙያዊ ድጋፍ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
ሁለት ትምህርት ቤቶችን የደረጃ ሽግግር እንዲያደርጉ ለማስቻል በልዩነት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተከናወነ መሆኑን አቶ የሻምበል ተናግረዋል፡፡
የጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በጊቢው ውስጥ ሞዴል የቅደመ አንደኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመክፈት ለማህበረሰቡ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሞዴል የቅደመ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መክፈት እጩ መምህራን በንድፈ ሃሳብ የሚማሩትን ትምህርት በተግባር እንዲመለከቱ እድል የፈጠረላቸው መሆኑን በግቢው ውስጥ የሚገኘው ሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደስታ ዓለሙ ገልጻለች፡፡
የኮሌጁ ከ50% በላይ መምህራን በጥናት እና ምርምር እንዲሳተፉ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በአሁን ሰዓት 19 ጥናት እና ምርምሮች እየተሰሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ የሚሰሩ ጥናት እና ምርምሮች በታዋቂ ጆርናሎች ለማሳተም እና ተግባር ላይ እንዲውሉ ለማስቻል እየተሰራ ነው፡፡
ኮሌጁ ህጻናት በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ ለማስቻል አንድ ሽህ ደብተር እንዲሁም አንድ ሽህ እስክብሪቶ ድጋፍ ማድረጉን የኮሌጁ ዲን አመላክተዋል፡፡
ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ማምረቻ ድርጅት አቋቁሞ ጥራታቸውን የጠበቁ የትምህርት መርጃ መሳሪዎችን እያመረተ እይገኛል፡፡ የኮሌጁ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ማምረቻ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ግርማ ገብረአምላክ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች ጥራታቸውን የጠበቁ የውስጥ እና የውጭ መጨወቻዎችን እያመረተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ ለኮሌጁ የገቢ ምንጭ እያስገኘ እና የስራ እድል እየፈጠረ ይገኛል።
የትምህርት መሳሪያዎች ድርጅት መኖሩ ከውጭ ይገቡ የነበሩ የሞንቶሰሪ እቃዎችን በመተካት ይወጣ የነበረን የውጭ ምንዛሬ የሚያሰቀር መሆኑን አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡
የውስጥ እና የውጭ መጫወቻ ቁሳቁሶቹ የአካባቢውን ባህል ያማከለ ልጆች በቀላሉ ሊማሩባቸው የሚችሉ መሆናችው ተገልጿል፡፡
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse



