የአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ቢሮ የ2018 ዓ.ም የ5 ወር እቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።
በግምገማው የ5 ወር የትምህርት እቅድ አፈፃፀም፣ የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት፣ የሴቶች እና ሕፃናት ትምህርት ተሳትፎ፣ የወጣቶች ተጠቃሚነት እንዲሁም በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ ችግሮች እና እድሎች በዝርዝር ቀርበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች የቀረበው ሪፖርት በትምህርት ላይ የደረሰውን ስብራት አገግሞ ወደ ነበረበት ለመመለስ የተሠራው ሥራ ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል።
ኾኖም ወደ ትምህርት ገበታቸው ያልተመለሱ ተማሪዎችን ከመመለስ፣ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ከመጠገን፣ የትምህርት ቁሳቁስ ከማሟላት፣ መምህራንን ብቁ ከማድረግ እና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማስጠበቅ አኳያ የሚቀሩ ብዙ ሥራዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ መድረኩ በ5 ወራት ውስጥ በጥንካሬ የተሠሩ ሥራዎችን የበለጠ ለማጠናከር ጉድለቶችን አስተካክሎ ለማስቀጠል የተፈጠረ መድረክ ነው ብለዋል።
በቀረበው ሪፖርትም በተያዘው በጀት ዓመት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል ነው ያሉት።
የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን በማስከፈት እና አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁስን ከማሟላት አኳያም ሰፊ ሥራ መሠራቱን ነው የተናገሩት።
የመጽሐፍ አቅርቦት ጥምርታን በተመለከተ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ አንድ ለአንድ ማዳረስ የተቻለ ቢኾንም ወደ ታች ያሉ ክፍሎች ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን መጻሕፍት በፌደራል መንግሥት መታተሙን ገልጸዋል።
በቀጣይ ያልተመዘገቡ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎችን በመመዝገብ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ ይጠበቅብናል ብለዋል።
እንደ አጠቃላይ የተሠሩ ሥራዎችን በማጠናከር እና ክፍተቶችን በማስተካከል ቀሪ ሥራዎች ላይ መረባረብ እንደሚገባም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሰ ቢሮው ያቀረበውን ሪፖርት ከማየት ባለፈ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር ምን ያክል ተጨባጭ ሥራዎች ተሠርተዋል የሚለውን የማረጋገጥ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
የቀረበው ሪፖርትም ቋሚ ኮሚቴው የተሠሩ ሥራዎችን ጥንካሬ፣ የታዩ ድክመቶችን እና በቀጣይ መሻሻል ያለባቸውን በግልፅ በመገምገም እና በማደራጀት ለምክር ቤቱ በማቅረብ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ እና አቅጣጫ እንዲሰጥበት ለማገዝ ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቢሮዎች በየጊዜው በሚሰጡት ግብረ መልሶች እና ማስተካከያ ሀሳቦችን በመያዝ ጉድለቶቻቸውን ለማስተካከል እድል ይሰጣል ነው ያሉት።
የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ግምገማ በየሩብ ዓመቱ እየፈፀመ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
አሚኮ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *