ማኅበረ ሕይወት ፎር ሶሻል ዴቨሎፕመንት የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በሦስት ትምህርት ቤቶች በ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የገነባቸውን እና ያደሳቸውን የመማሪያ ክፍሎች አስረክቧል።
የአማራ ክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የተገነቡ እና የታደሱ ትምህርት ቤቶችን ጎብኝተዋል።
በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በክልሉ በገጠመው የጸጥታ ችግር እና በሌሎች ምክንያቶች ተማሪዎች የሚገባቸውን አገልግሎት እያገኙ እንዳልኾነ ተናግረዋል።
ይህንን ችግር ለመሻገር ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የተሠራው ተግባር ደግሞ ሰብዓዊነትን ከማኅበራዊ ኀላፊነት ጋር ያጣመረ እና በአጭር ጊዜ የተሠራ ተግባር በመኾኑ ለሌሎች ልምድ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የፕሮጀክቶች ክትትል እና ግምገማ ባለሙያ መዝገበ አስማማው “በክልሉ ከ2 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች በግጭቱ ምክንያት በተለያየ ደረጃ ጉዳት እንደደረሰባቸው” ተናግረዋል፡፡
በዚህ ምክንያት የትምህርት ሥራው እንዳይበደል በደብረ ብርሃን ከተማ የተሠራው አይነት ተግባር ያስፈልጋል ብለዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ በከተማው ተፈናቃይ ተማሪዎች በሚገኙበት ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍል እና ቁሳቁስ ችግር ገጥሞ እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህ ምክንያት ሕጻናት በሸራ ዳስ ውስጥ ለመማር ተገደው ነበር ብለዋል።
የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸው ሕጻናት ተማሪዎች ደረጃውን በጠበቀ መማሪያ ክፍል ውስጥ በምቹ ወንበር እና ጠረንጴዛ ላይ እንዲማሩ ያስችላቸዋል ብለዋል።
ሕይዎት ሶሻል ዴቨሎፕመንት ሥራ አሥኪያጅ ጥላዬ ጌታቸው በከተማው የተፈናቃይ ተማሪዎች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለማቅለል ከሚሠራቸው የግንባታ ተግባራት በተጨማሪ የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎችንም እያደረጉ እንደኾነ ገልጸዋል።
ዘገባው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነው
ታህሳስ 14/2018

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *