።።።።።።።
ታህሳስ 13/2018 ዓ.ም (ትምህርት ቢሮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት መረጃ ስርአቱን በማዘመን ፈጣንና ጥራት ያለው የትምህርት መረጃ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል የተባለው አዲሱ ሲስተም ወደ ስራ መግባቱ ተነግሯል ።
በ2018 የትምህርት ዘመን በሀገር ደረጃ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ የሚደረገው ሲስተም በአማራ ክልል በሁሉም ትምህርት ቤቶች ለመተግበር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉ ታውቋል፡፡
በየደረጃው ለሚገኙ የትምህርት መረጃ ስርዓት የኤምአይኤስ እና የአይቲ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ ስልጠናዎች በመሰጠት ላይ መሆናቸውን በቢሮው የእቆድ ዝግጅት ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘመነ አበጀ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች አዲስ በበለጸገው ሲስተም በተሟላ ሁኔታ መረጃዎችን በማስገባትና መረጃዎችን ከዚህ የመረጃ ቋት ብቻ በመውሰድ መጠቀም እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አክለው ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት በጀትና የቁሳቁስ ድጋፎች እንዲሁም ከአለም ባንክ በኢቶል (ETOL) የሚደገፍ የትምህርት ቤት ድጎማ በጀት ከዚህ የመረጃ ቋት በተወሰደ የተማሪ ቁጥር መረጃ ብቻ እንደሚሆ ትምህርት ሚኒስቴር አሳውቋል፡፡
የትምህርት መረጃ አስተዳደር ሥርዓት የትምህርት ጥራትን እና ተደራሽነትን ለመገምገምና ለመንግስት የፖሊሲ ውሳኔዎች ትክክለኛ መረጃ ለማቅረብ ያለው ፋይዳ የጎላ ነው ተብሏል።
አዲሱ የትምህርት መረጃ አስተዳደር በተቋሙ ያሉ አጠቃላይ የተማሪዎች መረጃ፡ ምዝገባ፣ ውጤት እና የተማሪዎች ዝውውር እንዲሁም የመምህራን የትምህርት ደረጃ፣ የሥራ ልምድ እና ስርጭት የመሳሰሉ መረጃወችን የሚያካትት ሲሆን በትምህርት ቤቱ ያለውን አጠቃላይ የመሠረተ ልማት የመማሪያ ክፍሎች ብዛት፣ የቤተሙከራዎች እና የመጽሐፍት አቅርቦት መረጃወችን የሚያካትት ነው፡፡
የትምህርት ተቋሙን አጠቃላይ የፋይናንስ አጠቃቀምና ለትምህርት ቤቶች የሚመደብ በጀት ወጪና ገቢ በጀትን የሚያካትት የዘመኑ ቲክኖሎጅ ውጤት የሆነውን ሲስተም በአግባቡ በመጠቀም የመማር ማስተማሩን ስራ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *