“የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በትኩረት መስራት ይገባል”
የተከበሩ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018ዓ.ም የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀሙን ከምስራቅ ጎጃም፣ ደብረማርቆስ፣ ሰሜን ሸዋ እና ደብረብርሐን ከተማ አስተዳደር የትምህርት አመራሮችና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል።
በመድረኩም ያለፉት ስድስት ወራት የትምህርት ስራዎች አፈፃፀም በዝርዝር ቀርቧል። የቢሮው ስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሱፐርቪዥን ቡድን ግብረመልስና ተማሪዎችን ለማብቃት የተሰሩ ስራዎችና የቀጣይ የርብርብ ማዕከላት ሰነድ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አበራሽ ታደሰ በመድረኩ ተገኝተው ከቅድመ ዝግጅት እስከ ተግባር ምዕራፍ የትምህርት አመራሩ፣ ርዕሰ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች፣ ወላጆች፣ የትምህርት ማህበረሰቡ የትምህርትን ስራ ለማቃናት ያደረገውን ርብርብ አበረታች መሆኑን ገልፀዋል። ትምህርት ከገጠመው ስብራት ወጥቶ ወደ ከቀደምት ከፍታው ለመመለስ ሰፊ ስራዎች የተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በተለይም የክረምት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ግለሰቦች፣ ተቋማትንና ልዩልዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማሳተፍ የትምህርት ቁሳቁሶችን፣ የትምህርት ግብዓቶችን ለማሰባሰብና ለተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ የተደረገው ጥረት በረታች እንደሆነ ወ/ሮ አበራሽ ታደሰ አብራርተዋል።
በግምገማ መድረኩ ማጠቃለያና የቀጣይ አቅጣጫዎችን የሰጡት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ አሁን ላይ የሚታየውን ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴዎችና እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን የበለጠ ማላቅና ማጥለቅ ይገባል ብለዋል። ትምህርትን ከገባበት ቅርቃር ለማውጣት ከተለመደው አሰራር መውጣት፣ ኢነርጅ ጨምረን መስራት ይጠይቃል ሲሉ ተናግረዋል።
በመድረኩ በርካታ ተሞክሮዎች መቅረባቸውን ያነሱት ኃላፊው ተሞክሮዎችን በሁሉም አካባቢዎች ወስዶ ማስፋት የትምህርት አመራሩ ተግባር መሆን እንዳለበት ገልፀዋል።
በቀጣይም የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በትኩረት መስራት፣ የኦንላይን ፈተና ቅድመ ዝግጅት ስራዎች ፣ የተጀመሩ የትምህርት ፕሮጀክቶችን በጊዜ፣ በጥራትና ፍጥነት ማጠናቀቅ፣ የትምህርት ኢኒሸቲቮችን በተለይም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ስራዎች፣ የተማሪ ምገባና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ማስፋፋትና ራሱን ማስቻል እንዲሁም የትምህርት ዲጅታላይዜሽን ስራዎችን በተሟላ ሁኔታ መፈፀም፣ በ2018ዓ.ም የሚሰራውን የመርሱ ዝውውር በጥንቃቄና ውጤታማ በሆነ አግባብ መፈፀም፣ የኮሌጅ ትምህርት ቤቶች ግንኙነትን ማጠናከር፣ የEMIS መረጃ በወቅቱና በጥራት መሠብሰብ፣ በየደረጃው ካሉ መምህራን ማህበር አመራሮች ጋር ተቀራርቦ መስራት፣ የመፅሐፍት ስርጭትና አያያዝ ስራዎችን በጥንቃቄ መምራት፣ የድጋፍና ክትትል ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባና በሌሎችም አንኳር ጉዳዮች አቶ ጥላሁን ወርቅነህ አፅንኦት ሰጥተው አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን
5. በቲክቶክ ገፃችን @amharaeducation bureau



