።።።።።።።።
የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን መገንባት የትምህርት ጥራትን ለማስፋፋት፣ ተወዳዳሪ እና ብቃት ያላቸውን ተማሪዎችን ለማፍራት ያለው ሚና ጉልህ ነው።
በአማራ ክልል ደግሞ ይህን ፋይዳ ታሳቢ በማድረግ አሁን ላይ ሦሥት አዳሪ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃ ይገልጻል።
ከሚገነቡ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መካከል የሰቆጣ አዳሪ ትምህርት ቤት አንዱ ነው። ይህ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2016 ዓ.ም ነው በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት በሁለት ሥራ ተቋራጮች የግንባታ ሥራው የተጀመረው። በሁለት ዓመት ሠርቶ ለማጠናቀቅም እቅድ ተይዞለታል።
እየተገነባ የሚገኘው አዳሪ ትምህርት ቤት ቁጥራቸው 600 ተማሪዎችን ማስተናገድ የሚችል የተማሪ ማደሪያ ክፍሎች፣ የአሥተዳደር ሕንፃ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ዘመናዊ ሁለገብ ስታዲየም፣ ክሊኒክ፣ የውበት መጠበቂያ ሳሎኖች፣ ሱፐር ማርኬቶች እና መሰል አገልግሎት መስጫዎችን ያካተተ ነው።
የሎት አንድ ፕሮጀክትን እየሠራ የሚገኘው የመካሻ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ ሰማኽኝ ድጋፍ ፕሮጀክቱ ከተቀመጠለት የማጠናቀቂያ ጊዜ ቀድሞ ያለፈው መሥከረም ወር 2018 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ሲሠራ እንደነበር ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ አሁን ላይ 92 በመቶ ደርሷል ያሉት ሥራ አስኪያጁ የፀጥታ ሁኔታውን ተከትሎ የመጡ ችግሮች ባይኖሩ ኑሮ ቀደም ብሎ የመጠናቀቅ እድል እንደነበረው ነው የጠቀሱት። በቀጣይ ሁለት ወራትም ፕሮጀክቱን አጠናቀን እናስረክባለን ነው ያሉት።
የሎት ሁለት ፕሮጀክትን እየገነባ የሚገኘው የባማኮን ኢንጅነሪንግ ሥራ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር እሱባለው ሽፈራው በፕሮጀክቱ አሁን ላይ ጥሩ የሚባል የሥራ እንቅስቃሴ እንዳለ ተናግረዋል። ፕሮጀክቱን ከተቀመጠለት ጊዜ ሰሌዳ በፊት ለማጠናቀቅ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ መቆየታቸውንም አንስተዋል። ባለው የፀጥታ ሁኔታ እና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ግን በታሰበው ልክ አለመከናወኑን ጠቅሰዋል።
በሎት ሁለት በኩል የሚሠሩ ሥራዎችም 65 በመቶ መድረሳቸውን ነው የተናገሩት። ፕሮጀክቱ ትውልድ የሚፈራበት እና መንግሥት በጉጉት የሚከታተለው የሕዝብ ፕሮጀክት ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ በቀጣይ ነሐሴ ወር ለማጠናቀቅ እየሠሩ እንደኾነም አንስተዋል። ማኅበረሰቡ፣ የሚመለከታቸው የክልል እና የዞን ሥራ ኀላፊዎች ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ በክልሉ መንግሥት በጀት ሦስት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የሚገነቡ ትምህርት ቤቶች በ2019 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብለው እንዲያስተምሩ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነም አንስተዋል። እነዚህ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ሲጠናቀቅ በክልሉ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ቁጥርና የሚቀበሏቸው ተማሪዎች ተሳትፎ ይጨምራል ብለዋል፡፡ ይህም የክልሉን ተማሪዎች ውጤታማነት ትርጉም ባለው ደረጃ ያሻሽላል ነው ያሉት።
የአሚኮ



