በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ የሚገኘው የልማት በር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2015 ዓ.ም ካስፈተናቸው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት አነስተኛ ነበሩ።
ይህ ውጤት ያልተጠበቀ በመሆኑ የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ አስቆጭቷል። የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ሙሀባው ቸኮል ለውጤት ማሽቆልቆል ምክንያቶችን በመለየት የተማሪዎቹን ውጤት ለማሻሻል በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
ለተማሪዎች የተለዬ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ በመታመኑ ተማሪዎች በትኩረት እንዲያነቡ ትምህርት ቤቱ የአዳር ጥናት ማመቻቸት ላይ ትኩረት አድርጓል።
ትምህርት ቤቱ ለተመረጡ ተማሪዎች የምግብ፣ የመኝታ፣ የተለዬ የመምህራን ድጋፍ፣ የስነ ልቦና ስልጠና እና የ24 ሰዓት ቤተመጽሐፍት አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል።
ይህን በማድረጋቸው በ2017 የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤቱ የአዳር ጥናት የተሳተፉ 118 ተማሪዎች ሁሉም የማለፊያ ነጥብ አስመዝግበዋል።
በያዝነው ዓመት ከሚፈተኑ ተማሪዎች መካከል የተመረጡ ተማሪዎች በአዳር ጥናት እየታገዙ ናቸው።
በልማት በር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ የሆነው ተማሪ የአብስራ አማረ ትምህርት ቤቱ የምግብ፣ የማደሪያ ጨምሮ አስፈላጊ እገዛዎችን እያደረገለት በመሆኑ ሙሉ ጊዜውን ትምህርቱ ላይ አትኩሮ እያጠና መሆኑን ገልጿል።
ተማሪ መቅደስ ሲሳይ የትምህርት ቤቱን ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ አቅዳ እየሰራች ነው። የመምህራን እገዛ፣ ከጓደኞቿ ጋር በመተባበር የሚያካሂዱት የቡድን ጥናት፣ 24 ሰዓት የቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ማግኘት እና የወላጆቿ ድጋፍ ውጤት ለማስመዝገብ ብርታት እንደሚሆናት ገልጻለች።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክንዱ ዘውዱ በዞኑ በ15 ትምህርት ቤቶች ለ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች የአዳር እና ቡድን ጥናት ተመቻችቶ ለፈተና ቅድመ ዝግጅት እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከተማሪዎች፣ ከመምህራን፣ ከወላጆች እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠር ተማሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን



