በ34 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብር መጀመሩን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን የትምህርት ጥራትን እና ተሳትፎን ለማሳደግ በ16 ወረዳዎች የተማሪ ምገባ መርሐ ግብር መጀመሩን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
የምገባ ሥርዓቱ በ34 ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ የቅድመ መደበኛ እና ከ1 እስከ 4 ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ነው የተጀመረው፡፡
ከወረዳዎች እና ከማኅበረሰቡ በተገኘ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ምግባ እየተካሄደ መኾኑን የተናገሩት የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ ናቸው።
የምገባ ሥራውን ለማስፋት እና ለማጠናከር ወላጆች ለሕጻናት የመመገቢያ ቁሳቁስ እና የምግብ ወጭ ተሳትፎ እያደረጉ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
በዚህ የምገባ መርሐ ግብር መምህራንም ጭምር ከደመወዛቸው ድጋፍ ማድረጋቸውን ኀላፊው ገልጸዋል።
የምገባ መርሐ ግብሩን ለማሳለጥ በጤና፣ በሃብት ማሰባሰብ እና የልማት ሥራዎችን የሚከታተል ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋ።
የምገባ ሥራው ከሥርዓተ ምግብ ጋር የተሳሰረ እንዲኾን የትምህርት ቤቶችን መሬት በአትክልት እና ፍራፍሬ ለማልማት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቶች የሚያለሙት የጓሮ አትክልት ከምግብ ባሻገር የመማር ማስተማር ሥራውን የሚያጠናክር ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
የምገባ ሥራው እንዲቀጥል እና እንዲጠናከር ባለሃብቶች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ርብርብ እና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አቶ ጌታሁን አሳስበዋል።



