የአዳሪ እና ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ አለባቸው።
አቶ ጥላሁን ወርቅነህ
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ
ታህሳስ 21/2018ዓ.ም(ትምህርት ቢሮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ ግንባታቸው እየተካሄዱ ካሉት አዳሪ ትምህርት ቤቶች እና በፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር እየተገነቡ ካሉ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ተገኝተው የግንባታዎችን አፈፃፀም የገመገሙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ ክልሉ በገጠመው የሰላም ችግር ከትምህርት አኳያ ተሳትፎም ሆነ ፍትሐዊነቱ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ገልፀው ከዚህ ችግር ለመውጣት በተሰራው ስራ በትምህርት ዘርፉ ተስፋ ሰጭ ለውጦች እየመጡ ነው ብለዋል።
ኃላፊው አያይዘውም አሁን ላይ በክልሉ መንግስት በጀት ድጋፍ እየተገነቡ ያሉት የፍኖተ ሰላም፣ ደብረታቦር እና ሰቆጣ አዳሪ ትምህርት ቤቶች፤ በፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር በጀት ድጋፍ እየተገነቡ ያሉት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በክልሉ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሐይል ለመፍጠር የምናደርገውን ጥረት ለማሳካት ሚናቸው ጉልህ እንደሚሆነ ገልፀዋል።
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች እና ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታም በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለባቸው አቶ ጥላሁን ወርቅነህ በአጽኖት አሳስበዋል።
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታም ከ82% እስከ 32% ድረስ ያለ በመሆኑ አማካሪዎችና ኮንትራክተሮች በቀሪ ወራት በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ በመግባት በተያዘው በጀት አመት የትምህርት ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ በሚቀጥለው አመት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጿል።
በውይይቱም የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ፣ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች እና ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ተሳትፈዋል።



